The romantic comedy film is produced by Santos film production. Makda Afework who won best supporting actress in the film Sisit and Anibal Aberra played the lead role in the film.
Producer Anibal Aberra says it took 315, 000 birr to make the movie a success. The movie was in the making for 8 months.
The film which lasts for an hour and 41 minutes talks of romance between a software designer and his colleague.በሳንቶስ ፊልም ፕሮዳክሽን የተዘጋጀውና ከ100 በላይ ተዋናዮች የተሳተፉበት ‹‹ያ ልጅ›› የተባለው ፊልም የተመረቀው ሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2003 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ነበር፡፡ ፊልሙ ስኪዞፍሪኒያ በሚባለው የአእምሮ ሕመም አይነት የተጎዳ ልጅ ሕይወትን ያሳያል፡፡ የፊልሙ ፕሮዲውሰር ሀኒባል አበራ፣ ኤፍሬም የተባለውን የስኪዞፍሪኒያ ተጎጂ ልጅ ገጸ ባህሪይ ወክሎ ይጫወታል፡፡ ኤፍሬም ከማኅበረሰቡ ውስጥ ለየት ያለ ባህሪይ እንዳለው ተደርጎ የሚታይ ሲሆን፣ ቤተሰቦቹም ሆነ አብረውት ያሉት ሊረዱት አልቻሉም፡፡ ከሰዎች ጋር አለመግባባትና ማፈር የመሳሰሉ ባህሪያት የሚታዩበት ኤፍሬም ሥራውን በጣም ያፈቅራል፤ ሌት ተቀንም ይሠራል፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹ከላፕቶፑ ጋር የተጋባ›› በሚል ስም አንዳንዶቹ ሲጠሩት ይሰማል፡፡
ከኤፍሬም ጋር የምትሠራው ሃና ኤፍሬምን በጣም ትወደዋለች፡፡ ነገር ግን እሱ ከርሷ ጋር እንኳን አብሮ መሆን ቀርቶ ከሥራ ውጭ በሆነ ጉዳይ ሊያናግራት ፈቃደኛ አይደለም፡፡
በራሱ ዓለም ውስጥ መኖር የሚፈልገው ኤፍሬም የቤተሰቦቹ በተለይም የእናቱ ጭቅጭቅ የፈለገውን እንዲያደርግ የራሱን ምርጫም እንዲያደርግ እድል አልሰጡትም፡፡ በተለይም ብዙ ጊዜ የሚታመሙትን እና አግባ እያሉ የሚጨቀጭቁትን እናቱን ማምለጥ አልቻለም፡፡ በእነዚህ ግጭቶች መካከል ሆኖ ኤፍሬም ወደ ሴት መመልከት ይጀምራል፡፡
ፊልሙ የተጻፈውና ዳይሬክት የተደረገው በኃይሉ ዋሴ ሲሆን፣ ዳይሬክት የማድረጉ ሥራም የመጀመሪያው ነው፡፡
በፊልሙ ምርቃት የተገኘው የስርየት እና የፔንዱለም ፊልሞች ኤዲተር ያሬድ ሹመቴ፣ ኃይሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ዳይሬክት እንደማድረጉ አንዳንድ ክፍተቶች ቢታዩበትም ጥሩ አድርጎ እንደሠራው ይናገራል፡፡
የመሪ ተዋናይነቱን ሚና የተጫወተው ሀኒባል አበራ እና ሃናን ወክላ የተጫወተችው ብቃት ጥሩ እንደነበር ይገልጻል፡፡
‹‹ሀኒባል ፕሮዲዩሰር ብቻ ስለሆነ ሳይሆን በፊልሙ ላይ የተጫወተው ከእርሱ እውነተኛ ባህርይ የማይመሳሰል ገጸ ባህርይ ተጫውቶ ጥሩ አድርጎ መውጣቱ በሌላ ፊልሞች ላይም እንዲጫወት ያስችለዋል፡፡››
ለያሬድ ከሀኒባል በተጨማሪ ማክዳ የተሰጣትን ገጸ ባህርይ ጥሩ አድርጋ የተጫወተች ሲሆን፣ ለወደፊቱም ጥሩ ተስፋ እንዳላት ይናገራል፡፡
‹‹ብዙ ጊዜ ፊልሞች ላይ ሆን ተብለው የሚመረጡት ረዘም ያሉና ቀጠን ያሉ ሴቶች ሲሆኑ፣ ማክዳ ግን አጠር ብላ ወፈር ያለች ነች፡፡ እስካሁንም ሌላ ፊልሞች ላይ ሲሰራ የነበረውን አስተያየት መስበር ወይም መቀየር ችላለች፡፡››
ለያሬድ በጣም ያሳዘነውና ያላስደሰተው ነገር ቢኖር በፊልሙ የራሱ የሆነ ሙዚቃ (ስኮር) አለመጠቀማቸው እንደሆነ ይናገራል፡፡
ፊልሙ ላይ የውጭ አገር ሙዚቃዎች እንደማጀቢያነት መግባታቸውና፣ በተፈጥሮ ሊሸፈኑ የሚገባቸው እንደ የመኪናና የወፎች ድምጽ ዓይነቱ በሙዚቃ መሸፈናቸው ምን ያህል ለድምጽ ትኩረት እንዳልተሰጠ አሳይ ነውም ይላል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ጠቃሚ ያልሆኑ የጎን ታሪኮች ለያሬድ መግባታቸው የፊልሙ አንድ ጉድለት እንደሆነ ይገልጻል፡፡
አንዳንድ የቤት ውስጥ ቀረጻዎች ጨለማ መሆናቸው፣ በምልሰት ሊገለጹ የሚችሉ ደግመው መታየታቸው ከልምድ ማነስ የመጣ መሆኑን ያሬድ ይናገራል፡፡
ብዙ የአማርኛ ፊልሞች ለሚያየውና ለሚያደንቀው ቢንያም ከበደ ፊልሙ ካስደሰቱት ፊልሞች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ ታሪኩ ቀለል ያለ መሆኑ፣ ከማሳቅ ጋር ቁም ነገር ማስተላለፉ ‹‹ያ ልጅ›› ን እንዲወደው አድርጎታል፡፡
‹‹በጣም የሚያፍሩ ልጆችን ማንም አይረዳቸውም፡፡ ይሄ ፊልምም እንደ አንድ ጉዳይ አንስቶ ማሳየቱ ጥሩ ነገር ነው፡፡››
በፊልሞች ምርቃት ላይ እንደምትገኝ የምትገልጸው የ31 ዓመቷ ራሔል እሸቱ በዚህም ፊልም ላይ ተገኝታ ፊልሙን የተመለከተች ሲሆን፣ ከፊልሙ ምርቃት መንዛዛት በተጨማሪ የፊልሙ ታሪክ ሊዋጥላት እንዳልቻለ ትናገራለች፡፡
በተለይም ከስኪዞፍርኒያ ጋር በተያያዘ በትወናው የቀረበው ከእውነታው የራቀ በመሆኑ ባለሙያ አማክረዋል ብላ እንደማታስብ ትናገራለች፡፡ ‹‹ስኪዞፍሪኒያ የምንለው ብዙ ምልክቶች ያሉት ሲሆን፣ ከእነሱ ውስጥ ለምሳሌ ያህል በማንኛውም ጊዜ ምንም ዓይነት ስሜት አለመሰማት፣ የትኛውንም ሥራ አለመጨረስ፣ ድምጽ መስማት ወይም ምስል ማየት የተወሰኑት ናቸው፡፡ በፊልሙ ላይ ግን በሥራው ጎበዝ የሆነ የሚያፍር ልጅ ሕይወት ይታያል፡፡ ለወደፊቱ ያስባል፡፡ ስለቤተሰቦቹም ይጨነቃል፡፡ በምን ዓይነት መስፈርት ልጁ ስኪዞፍሬኒክ እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡››
‹‹ያ ልጅ››ን ሰርቶ ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት ያህል ፈጅቷል፡፡